TM Law Firm Accessibility
×
ምክር ቤቱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርአት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፀደቀ

ምክር ቤቱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርአት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፀደቀ

መጋቢት 24፣ 2018 ዓ.ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ13ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርአት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ  ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት የወንጀል ፍርድ ሂደት የተጠርጣሪን እና የተከሳሽን እንዲሁም በወንጀል ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር የሕግ የበላይነት በማስፈን የአሰራር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

የተቀላጠፈ የፍትህ ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል እና ልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴን እንዲሁም ለተጎጂዎች ካሣ የሚከፈልበትን አግባብ ያካተተ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ ረቂቅ ሕግ እንደሆነ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ  አያይዘው አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ ከኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ መርሆች እና እሴቶች እንዲሁም ከወንጀል ህጉ ጋር የተጣጣመና ዘመናዊ በመሆኑ ጠቀሚ እንደሆነ  ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡

ረቂቅ ህጉ በህገ መንግስቱ፣ በወንጀል ሕጉ፣ ዓለም አቀፍ ህጎች እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ህጎች የተረጋገጡ ልዩ ትኩረት ለሚያሻቸው ለሴቶች፣ ህፃናት እና አካል ጉዳተኞች የተሰጣቸውን መብቶች ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነም የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ረጅም ጊዜ የቆየና የዘገየ ቢሆንም በህዝቡ ዘንድ የቅሬታ ምንጭ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ወቅቱን የሚመጥን አዋጅ በመሆኑ የህዝብን የፍትህ ሥርዓቱን ለማስፈን እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የዜጎችን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲአዊ መብቶችን ለማስከበር እና የፍትህ ሥርዓቱን በማዘመን ወቅቱን ያዋጅ አግልግሎት ለመስጠት ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን የምክር ቤት አባላት አመላክተዋል፡፡፡

በሌላ በኩል የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ በአተገባበር ሂደት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ ከፍትህ አካላት ጋር መወያየት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ከምርመራ ሂደት እና ከዲጂታል አሰራሮች ጋር በተያያዘ ዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብትን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት የምክር ቤት አባላቱ አስገንዝበው፤ በማረሚያ ቤት ቆይተው ፍርድ ቤት ነፃ የሚላቸው ዜጎች የካሳ ክፍያ ሥርዓትን ለመዘርጋት በግልጽ በረቂቅ አዋጁ ማስቀመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርአት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ፤ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 አድረጎ በሁለት ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡